በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት መንግስታዊ ካልሆኑ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት መካከል አንጋፋ የሆነው የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር 32ኛውን ጠቅላላ ጉባዔውን ግንቦት 22 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ሳሮ ማሪያ ሆቴል አካሂዷል፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዴንት ዶክተር ትዝታ ጎሳ ጉባኤውን በንግግር ከፍተዋል፡፡ የጉባኤው ተሳታፊዎች እ.ኤ.አ በ2020 በስራ አስፈጻሚ ቦርድ፣ በአቃቤ ንዋይ፣ በፕሮግራም፣ በፋይናንስ እና በውጭ ኦዲተሮች የቀረቡላቸውን ሪፖርቶችና አዳምጠዋል፡፡ በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይቶች ከተደረገ በኋላ አስተያየት ተሰጥቶባቸው በጠቅላላ ጉባኤው ጸድቀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የማኅበሩ የ2021 የበጀት ዓመት እቅድ ላይ በጉባኤተኞች ውይይት የተደረገ ሲሆን አስተያየት ተሰጥቶበት እንዲጸድቅ ተደርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላላ ጉባዔው የ2021 የውጭ ኦዲተር ለመመልመልና ለመቅጠር እንዲቻል ለስራ አስፈጻሚ ቦርዱ ውክልና ሰጥቷል፡፡
በመጨረሻም የማህበሩን ፕሬዚደንት፣የጠቅላላ ጉባኤ ስራ አስፈፃሚ አባላት እና የዋና ስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት በጠቅላላ ጉባዔው ተመርጠዋል፡፡ ማኅበሩን ለቀጣይ አራት ዓመታት በፕሬዚዴንትነት እንዲመሩ ዶክተር ወንድወሰን አሰፋ በጠቅላላ ጉባዔው ተመርጠዋል፡፡ ዶክተር ወንደሰን አሰፋ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በህክምና (ሜዲካል ዶክተር) ያገኙ ሲሆን ሁለተኛ ድግሪያቸውን ደግሞ በጤና ኢኮኖሚክስ ይዘዋል፡፡ ማህበሩን በምክትል ፕሬዚዴንትነት እንዲያገለግሉ ደግሞ ወ/ሮ ቤቴልሄም ታየ በጠቅላላ ጉባዔው የተመረጡ ሲሆን የመጀመሪ ድግሪያቸውን እና ሁለተኛ ድግሪያቸውን በማህበረሰብ ጤና ይዘዋል፡፡