የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር የኢትዮጵያ መንግስት በየጊዜው የሚያወጣቸውን አዳዲስ የጤና ፖሊሲዎችንና ስትራቴጀዎች ተግባራዊነት በማገዝ በኩል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ማኅበር መሆኑ ተገለፀ። ይህም የተገለጸው የአዲስ አበባ አካባቢ ጽ/ቤት 30ኛ አመታዊ የበጎ ፍቃደኞች ስብሰባ ባካሄዱበት ወቅት ነው ። ማኅበሩ ባለፉት 56 ዓመታት ጉዞው በጤናው ዘርፍ ከመንግስት እና ከአጋርሮቹ ጋር በጋራ በመስራት፣ የጤና ባለሙያዎችን አቅም በማጎልበትና ህብረተሠቡን በተለይም ወጣቱን የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ዙሪያ ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት የእለቱ የክብር እንግዳ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሀላፊ ተወካይ አቶ አለማዬሁ ወንድሙ ናቸው፡፡ የአካባቢ ጽ/ቤቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚሠጠው አገልግሎት የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ ድጋፍ እንደማይለየው አቶ አለማየሁ ቃል ገብተዋል። በጉባኤው የ2021 እ.ኤ.አ ዓመታዊ የስራ አፈፃፀም ፤ የወጣቶች የስራ እንቅስቃሴ ሪፖርት እንዲሁም የአካባቢ ጽ/ቤቱ አማካሪ ቦርድ አመታዊ የስራ አፈፃፀም ለጉባኤው አባላት ቀርበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአገልግሎት ጊዜያቸውን የጨረሱ የስራ አስፈፃሚ አባላቶች በምርጫ ተካሂዷል፡፡ የማህበሩ ኘሬዚዳንት ዶ/ር ወንዶሠን አሠፋ ለጉባኤው የስራ መመሪያ በመስጠት፣ ለማህበሩ የእድሜ ልክ አባላትና እና ለድርጅት አባላቶች የእውቅና ሰርቲፊኬት በመስጠት ጉባኤ ተጠናቋል።