የማዕከላዊ አካባቢ ጽ/ቤት 29ኛ አመታዊ ጉባኤውን በአዳማ ከተማ በ17/07/2014 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ የማኅበሩ ዋና ስራ አሰኪያጅ አቶ ጌታቸው ሀብቴ በመልካምና አርቆ አስተዋይ በጎ ፍቃደኞች የተመሠረተው ማኅበር ለ56 ዓመታት የተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ማኅበሩ የተዋልዶ ጤናን አገልግሎት በሀገሪቱ የጀመረ፤ መንግስት በጤና ኤክስቴሽን ኘሮግራሙ የሚሠጠውን አገልግሎት በህብረተሰብ አቀፍ ጤና አገልግሎት ሰጭ በጎ ፍቃደኞች መነሻ እንዲሆን መንገድ የከፈተ፤ ለመንግስትና ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት ለተቋቋሙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም አርአያ እንደሆነ ያነሱት አቶ ጌታቸው ማኅበሩ በርካታ ተግዳሮቶችን አልፎ አሁን ላለበት ደረጃ የደረሠ አንጋፋ ድርጅት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ማህበሩን ባላቸው እውቀት፤ ጉልበት እና ሀብት የሚያግዙ 20,000 በጎ ፍቃደኞቹን ይበልጥ ማህበሩን ሊያግዙበት የሚችሉበትን ዲጅታል የትስስር ገፆችን የሚዘረጋበት መንገድ መፍጠር አሰፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግ ዋና ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩልም የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ከበደ ፈይሳ የአሠላ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ሀላፊ ተወካይ ማህበሩ በተዋልዶ ጤና ችግሮች ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማኀበረሰብ ክፍሎች ማለትም ሴተኛ አዳሪዎችን፤ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን እና በተለያዩ ምክንያቶች ከመረጃና አገልግሎቶች የራቁ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያደርጋቸው ጥረቶት የመንግስትን ስራ የሚደግፉ ናቸው ብለዋል ።
በጉባኤው የ2021 እ.ኤ.አ. የማዕከላዊ አካባቢ ጽ/ቤት ዓመታዊ የስራ ሪፖርት በጽ/ቤቱ ሀላፊ አቶ ጋሻው ከበደ የቀረበ ሲሆን በጉባኤተኛው አሰተያየት ተሠጥቶበታል። ከዚህ በተጨማሪም የአካባቢው ጽ/ቤት አማካሪ ቦርድ የስራ አፈፃፀም በሰብሳቢው በአቶ ዳንኤል ገ/ፃዲቅ ቀርቧል፡፡
በመጨረሻም የኢትዬጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር ኘሬዚዳንት ተወካይ እና የማኅበሩ የወጣቶች ተወካይ ወጣት ሀዊ ሽመልስ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ወጣቶች የተዋልዶ ጤና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ወደ ኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር የወጣት ማዕከሎች ከመምጣት ባሻገር ማኅበሩ ወጣቶች ወዳሉበት ቦታ በመሄድ አገልግሎቱን ማድረስ እንደሚገባው ገልፀዋል።